ኢትዮጵያ በትራምፕ የህዳሴ ግድብ አስተያየት ላይ ያለመ የተቃውሞ ፊርማ ልታሰባስብ ነው

የህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ግብፅ የህዳሴ ግድብን ታፈነዳዋለች" የሚልና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ አሉታዊ አስተያየቶችን መስጠታቸውን በመቃወም ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የተቃውሞ ፊርማ ማሰባሰብ ልትጀምር ነው።

ስነ ስርአቱ በዛሬው ዕለት ጥቅምት 21፣ 2013 ዓ.ም በግዮን ሆቴል 10 ሰዓት ላይ እንደሚጀመርም በዋነኝነት ይህንን ፊርማ የማሰባሰብ ስራ የሚመራው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

የፅህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት የሚዲያ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም ፊርማው በበይነ መረብ (ኦንላይን) የሚካሄድ ሲሆን ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግብፅ የህዳሴ ግድብን ታፈነዳዋለች ለሚለው አፀፋዊ የተቃውሞ ምላሽ መሆኑንም ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ከዛሬ ጥቅምት 21፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ ባሉትም አራት ቀናት ኢትዮጵያውያን የፕሬዚዳንቱን ንግግር ፊርማቸውን በማኖር እንዲቃወሙ ጥሪ የቀረበላቸው ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ለሚመለከታቸው አገራት ደግሞ ትኩረት እንዲሰጡትም ያለመ መሆኑንም አቶ ኃይሉ ያስረዳሉ።

በነዚህ አራት ቀናትም ውስጥ እስከ 150 ሺህ ፊርማ የማሰባሰብ እቅድም ተይዟል።

በተለያዩ አገራትም በርካታ ሰዎችም በቡድን ሆነ በተናጠል የተቃውሞ ፊርማዎችን ማሰባብ መጀመሩን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ የህዝብ ጥያቄ አይሎ በመምጣቱና ፅህፈት ቤቱም ህዝባዊ ተሳትፎ በቀጥታ የሚመለከተው በመሆኑ አንድ ወጥ በሆነና የበለጠ በተጠናከረ መልኩም ለማገዝም እንዳለመ ይናገራሉ።

የዶናልድ ትራምፕ ንግግር "ፀብ የሚጭር ነው" ያሉት አቶ ኃይሉ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የአለም ሰላም ወዳድ ህዝቦችም በዚህ ሊሳተፉ እንደሚችሉም ጠቆም አድርገዋል።

"ኃላፊነት የጎደለውና ግልፅ የሆነ ለአንድ ወገን ያዘነበለና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚነካና የሚሸረሽር ተናግረዋል። ይህም ንግግር በአገር ውስጥም ሆነ በተለያየ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ዳር እስከ ዳር አስቆጥቷል።" ብለዋል።

"ንግግራቸው በአፍሪካም ሆነ በቀጠናው ያለውን ሰላም የሚያናጋ ነው" በማለትም አክለዋል።

ግብጽ በጎርጎሳውያኑ 1959 የተፈረመውና፣ የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት አጥብቃ በመያዝ ታሪካዊ ተጠቃሚነት በሚል መርህ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት አላት የምትለው ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባውም ለፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነትም መሆኑንም ትናገራለች።

ባልነበረችበት የተፈረመ ስምምነት ለናይል ወንዝ 77 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ለምታመነጨው ኢትዮጵያ ምንም ድርሻ የማይሰጥና ተፈጥሯዊም ሆነ ሕጋዊ መብቴን የሚነጥቅ ነው በማለትም ኢትዮጵያ ትከራከራለች።

አቶ ኃይሉ እንደሚሉት የግድቡ ግንባታ ከዚያ ባለፈ የቀጠናው የሰላም ምንጭ ነው ይላሉ ለዚህም እንደ አባሪነት የሚያነሱት ከአፍሪካ ህብረትም ርቃ የነበረችው ግብፅ በህብረቱ አደራዳሪነት የሶስትዮሽ ድርድር እያካሄደች መገኘቷን በመጥቀስ ነው።

በብዙ ነጥቡም የሶስትዮሽ ድርድሩ ላይ መግባባት ላይ መደረሱንም አክለው ይገልፃሉ።

በዋናነት ይህንን ፊርማ በማሰባሰብ ከሚያስተባብረው ፅህፈት ቤት በተጨማሪ ሊፍት ኢትዮጵያ፣ ጀስቲስ ፎር ሂውማኒቲ የሚባሉ ድርጅቶችም ፊርማውን በማሰባሰብ አብረው ይሰራሉ።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥቅምት 13፣ 2013 ዓ.ም ሱዳን እና እስራኤል ግንኙነታቸውን ለማደስ የደረሱበትን ስምምነት አስመልክቶ ከሱዳን ጠቅላይ ምኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ እና ከእስራኤሉ ጠቅላይ ምኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር በስልክ በተነጋገሩበት ወቅትም ነው የህዳሴ ግድብን ጉዳይን ያነሱት።

"ግብፅ በዚህ መንገድ መቀጠል ስለማትችል ሁኔታው አደገኛ ነው። ግብፅ የህዳሴ ግድብን ታፈነዳለች፤ አሁንም በግልፅ እናገረዋለሁ ግብፅ በድጋሚ ታፈነዳዋለች" በማለት በተደጋጋሚ የተናገሩት ትራምፕ

"ስምምነት ለአገራቱ ባቀርብም ኢትዮጵያ ስምምነቱን ሳትቀበል ቀርታለች። አንደዚያ ማድረግ አልነበረባቸውም ይህ ትልቅ ስህተት ነው። በዚህም ምክንያት የምንሰጣቸውን ብድር አቁመናል። ስምምነቱን ካልተቀበለች በስተቀር ኢትዮጵያ ያንን ገንዘብ አታየውም " ማለታቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮች እንዲሁም የሕግ እና የውሃ ጉዳይ የቴክኒክ ባለሞያዎች በዋሽንግተን ዲሲ ሲደራደሩ በነበረበት ወቅት በዓመታት የተራዘመ ድርቅ እንዲሁም በተራዘመ ዓመታት አነስተኛ የውሃ ፍሰት ላይም መሰረታዊ መግባባት ተደርሷል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ያለምንም ውጤት መቋረጡ ይታወሳል።

በወቅቱም ግብጽ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቴን ይቀንሰዋል እንዲሁም ለእርሻ የሚያስፈልገኝ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በየዓመቱ ይገባኛል ስትል የቆየች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በበኩሏ 31 ቢሊዮን ኪዩቡክ ውሃ በዓመት ለመልቀቅ ሃሳብ አቅርባ ነበር።

ነገር ግን አሜሪካ በበኩሏ 37 ቢሊዮን ኪዩብክ ሜትር እንዲለቀቅ መጠየቋ ተነግሮ ነበር።

ኢትዮጵያ ወንዙ በግድቡ ስፍራ እንደሚኖረው ዓመታዊ የፍሰት መጠን ከ4 -7 ዓመታትን በሚወስድ የሙሌት ደረጃ ግድቡን የመሙላት እቅድን ብታቀርብም ግብፅጽ በበኩሏ ጥቅሜን የሚጋፋ ነው በማለት ከ12 እስከ 21 ዓመታት መውሰድ አለበት ትላለች።

ኢትዮጵያ ዋሽንግተን ሲካሄድ የነበረውንም ድርድር ያቋረጠችበት ምክንያት በግብጽ ፍላጎት ታዛቢ እንዲሆኑ የገቡት አሜሪካና የዓለም ባንክ ለግብጽ ከመወገን አልፈው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ላይ ጫና ለማሳደር ሞክረዋል በማለት ኢትዮጵያ መውቀሷ የሚታወስ ነው።

አሜሪካ፣ የዓለም ባንክ ከግብጽ ጎን ቆመው ነበር በተባለው በዚህ ድርድር ላይ ከመጀመሪያው ሙሌት በኋላ ኢትዮጵያ ለምትጠቀመው ውሃ ለግብጽ የተጠራቀመ የውሃ ጉድለት ማካካሻ እንድትሰጥ የሚያስገድድ እንደሆነም ተገልጾ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ የግብጽ ሃሳብ በአባይ ወንዝ ላይ ተፈጥሯዊ መብት እንዳይኖራት ወይም ምንም ዓይነት የውሃ ልማት ያልተገነባበት ፍሰት እንዲኖር የሚጠብቅ ነው በማለትም ትተቻለች።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ይህንን ማለታቸውን ተከትሎም በግድቡ ዙሪያ የሚሰጡ ማስፈራሪያዎች ከመረጃ ክፍተት የሚነሱ፣ ውጤታማ ያልሆኑ እና የዓለም አቀፍ ሕግን የጣሱ እንደሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ ሰጥቷል።

ከዚህም በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ ተቀማጭ የሆኑትን የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሬይኖርን ጠርተው ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋቸዋል።

በርካቶችም ቁጣቸውን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በመግለፅ ላይ ሲሆኑ ፤ የተቃውሞ ሰልፎችም ተካሂደዋል።

በዩናትድ ኪንግደም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የትራምፕን አስተያየት በመቃውም ለንደን በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት ነው ሰልፍ በትናንትናው ዕለት አካሂደዋል።

በተለያዩ አገራትም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማምጣትም እየሰሩ መሆናቸውንም አቶ ኃይሉ ይናገራሉ።