ደቡብ አፍሪካ፡ "የአባቴን ገዳይ አቅፌው አለቀስኩ"

ካንዲስ ማማ

የፎቶው ባለመብት, CANDICE MAMA

ካንዲስ ማማ ትባላለች፡፡ ደቡብ አፍሪካዊት ናት፡፡

9 ዓመቷ ላይ ሳለች አንድ ጥፋት አጠፋች፡፡

እናቷ ገበያ ስትሄድ ቀስ ብላ የእናቷ መኝታ ቤት ገባች፡፡ እዚያ ቁምሳጥን አለ፡፡ ቁምሳጥኑ ላይ መጽሐፍ አለ፡፡ ልትደርስበት አልቻለችም፡፡ ትንሽ ልጅ ነበረች፡፡ ወንበር ላይ ተንጠለጠለች፡፡ ከዚያም ለዓመታት ተደብቆ የሚቀመጠውን መጽሐፍ ከቁምሳጥኑ አናት ላይ አወረደችው፡፡ ከዚያም ቶሎ ቶሎ ማንበብ ጀመረች፡፡

ሕይወቷ ያን ቀን ፈረሰ፡፡ ባየችው ነገር ተረበሸች፡፡ ጤና ራቃት፡፡ ምናለ ያን ቀን ያን መጽሐፍ ባልገለጠች ኖሮ?

ያባቷን ገዳይና የአባቷን ሬሳ ነበር መጽሐፉ ውስጥ የተመለከተችው፡፡

ካንዲስ ማማ ከዚያን ቀን ጀምሮ እያደገች እያደገች አሁን ትልቅ ሰው ሆናለች፡፡ ጸጸት ግን እየገዘገዛት ነው የኖረችው፡፡ ምናለ ያን መጽሐፍ ያን ዕለት ባልገለጠችው ኖሮ!

ምስጢራዊው መጽሐፍ

ካንዲስ ማማ ገና 8 ወሯ ሳለች ነበር አባቷ የሞተው፡፡ ስለዚህ በቅጡ አባቷን አታውቀውም፡፡ ሰዎች ስለአባቷ ሲያወሩ ግን ትሰማለች፡፡

አባቷ ሕይወትን ቀለል አድርጎ የሚመለከት፣ መደነስና መጫወት የሚወድ፣ ሙዚቃ ሲሰማ ዘሎ ወደ መድረክ የሚወጣ ዓይነት ሰው ነበር፡፡

ይሳቅ ይጫወት እንጂ በመብት ጉዳይ ቀልድ አያውቅም ነበር፡፡ የፓን አፍሪካን ኮንግረስ አባል የሆነውም ለዚሁ ነበር፡፡

በምህጻረ ቃል ፓክ የሚባለው ይህ የፖለቲካ ፓርቲ ከነ ማንዴላ፣ ከነ ሲሱሉ፣ ከነ ኦሊቫር ታምቦ ተገንጥሎ የወጣ ነበር፡፡

ይህ ፓርቲ ለጥቁሮች የቆመ ቢሆንም እነ ማንዴላ እኩልነት ቅብርጥሶ የሚሉት ነገር አይመቸውም፡፡ ‹‹ደቡብ አፍሪካ የጥቁሮች መሬት ናት፤ ኻላስ፡፡ ነጮች ከአገራችን ይውጡ፣ በቃ›› ይላል፡፡

የካዲስ አባት ጥቁሮች ከአፓርታይድ ጭቆና ነጻ እንዲሆኑ የሚመኝበት መንገድ ከነማንዴላ ጋር ቢቃረንም ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እጅና ጓንት ሆኖ ሲታገል ኖሯል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ግን እርጉሙ፣ ነፍሰበላው፣ ጭራቁ በሚሉ ቅጽሎት በሚታወቀው የአፓርታይዱ ጌታ ዩ ጂን ዲኮክ እጅ ወደቀ፡፡

ካንዲስ ማማ ሕጻን እያለች

የፎቶው ባለመብት, CANDICE MAMA

ዩ ጂን ዲኮክ ማን ነው?

ዩ ጂን ዲኮክ በደቡብ አፍሪካ አሁንም ድረስ ስሙን ሲሰሙ የሚንዘረዘሩ አሉ፡፡ ገራፊ ብቻ ሳይሆን የገራፊዎች አለቃ ነበር፡፡ ለጭካኔው ልክ የለውም፡፡ በአፓርታይድ ምድር ማንም እንደ ዩ ጂን ዲኮክ ያለ ክፉ የለም ይላሉ፡፡

የወንድ ብልት ላይ ድንጋይ አንጠልጥሎ፣ የውስጥ እግር ገልብጦ የሚተለትል የስቃይ ቡድን መሪ ነበር ዲኮክ፡፡

የካንዲስ ማማ አባት በዚህ ነፍሰ በላ እጅ ነበር የወደቀው፡፡

ካንዲስ ከልጅነቷ ጀምሮ አባቷ በሆነ ሰው እንደተገደለ ትጠራጠር ነበር፡፡ የአባቷ ገዳይ ግን ዩ ጂን ዲኮክ ነው ብላ በጭራሽ አላሰበችም፡፡

የፈረንጅና የጥቁር ቅልቅል የሆነችው እናቷም ይህን ጉድ ነግራት አታውቅም፡፡ በደቡብ አፍሪካ ክልሶች ከለርድ ይባላሉ፡፡ እናቷ ከለርድ ነበረች፡፡

ልጅ እያለች ግን አንድ ነገር ትዝ ይላታል፡፡ ሁልጊዜም ዘመድ አዝማድ ቤት ከመጣ በኋላ ያቺ ከኮሞዲኖው ጀርባ የምትደበቀው መጽሐፍ ትወጣለች፡፡ ከዚያ ያቺን መጽሐፍ ሰዎች ገልጠው ከተመለከቱ በኋላ ያለቅሳሉ፡፡

ይህ ነገር ሲደጋገም በጣም እየገረማት መጣ፡፡ ለምንድነው ሰዎች ይህን መጽሐፍ ገልጠው የሚያነቡት(የሚያለቅሱት)? ለምን መጽሐፉን ሳይገልጡ አያለቅሱም ግን?

ይህ አእምሮዋን እረፍት የነሳውን ጥያቄ ለመመለስ ነበር ልክ 9 ዓመት ሲሞላት የእናቷን ገበያ መሄድ አስታካ ቶሎ ብላ ያን መጽሐፍ የገለጠችው፡፡

መጽሐፉ በውስጡ የያዘው የገራፊዎችንና የገዳዮችን ኑዛዜ በፎቶ አስደግፎ ነበር፡፡ መጽሐፉ ‹‹ኢንቱ ዘ ሀርት ኦፍ ዳርክነስ፤ ኮንፌሽን ኦፍ አፓርታይድ አዛዚንስ›› (Into the Heart of Darkness - Confessions of Apartheid's Assassins) የሚል ርእስ ያለው ነው፡፡

በዚህ ርእስ የአባቷን ገዳይና ሬሳ ብቻ አልነበረም ያየችው፡፡ አገዳደሉንም ጭምር እንጂ፡፡ አባቷ የመኪናውን መሪ እንደተደገፈ በጥይት ተደብድቦ ሰውነቱ ተቃጥሎ ነበር በዚያ ፎቶ ላይ የሚታየው፡፡

ይህ ምሥል እድሜ ዘመኗን ሲያንዘፈዝፋት ኖረ፡፡ ከ9 ዓመቷ ጀምሮ፡፡

የሆነ ዕድሜ ላይ ስትደርስ ራስን ስለማጥፋት ማሰብ ጀመረች፡፡ የሆነ ቀን ልቧ መምታት ያቆመ መሰላት፡፡ የልብ ሕመም ስለመሰላት ሐኪም ቤት ሄደች፡፡

የሆነ ቀን ምሽት 16 ዓመቷ ላይ ራሷን ሳተች፡፡ ሆስፒታል ሐኪሟ ነገሩ እንግዳ ሆኖበት አገኘችው፡፡

በሷ እድሜ ሰዎች የልብ ድካም ሊያጋጥማቸው የሚችልበት እድል ጠባብ ነው፡፡ ምናልባት የሚያስጨንቅሽ ነገር ይኖር ይሆን ተባለች፡፡

ሐኪሙ ‹‹እኔ ባለፉት 20 ዓመታት እንዲህ ዓይነት ነገር ገጥሞኝ አያውቅም፤ ሕይወትሽን በገዛ ጭንቀት አፍነሽ ልታጠፍያት ተቃርበሻል›› አላት፡፡

በዚህን ጊዜ ነበር ስለ አባቷ ገዳይ ላለፉት በርካታ አመታት የተብሰለሰለችውን ነገር ልጓም ትታበጅለት እንደሚገባ የወሰነችው፡፡

ዩጂን ዲኮክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ገዳይን አቅፎ ማልቀስ

በ1995 ማንዴላ ሥልጣን ሲይዙ የእርቅና እውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ተቋቁሞ ነበር፡፡

ይህ ኮሚሽን በአፓርታይድ ዘመን ግፍ የተፈጸመባቸውን ሰዎች መረጃ ማሰባሰብ፣ ፈጻሚዎችንም ለሕግና ለእርቅ ማቅረብ ነበር ዓላማው፡፡

የአባቷን ገዳይ ዲኮክን ማፈላለግ ጀመረች፡፡ ስለሱ ብዙ አነበበች፡፡ የተናዘዛቸውን ግድያዎች በብዙ አግበስብሳ አነበበች፡፡ እያነባች፡፡

ከዚያ አንድ አዲስ ስሜት ተሰማት፡፡ እሷ መኖር የምትችለው ይህንን ነፍሰ በላ ስትገድለው ነው፡፡ ሌላው ለመኖር ያላት አማራጭ ደግሞ ከልቧ ይቅር ስትለው ነው፡፡

‹‹ይቅር የምለው ለኔም ለሱም ብዬ ነው፡፡ እየተበቀልኩትም ሊሆን ይችላል፡፡ አባቴን ባሰብኩ ቁጥር ይህንን ነፍሰ በላ አስበዋለው፡፡ እሱን ባሰብኩ ቁጥር ስሜቴን እሱ ይቆጣጠረዋል፡፡ በዚህን ጊዜ እታመማለው፡፡ እኔ በሱ ቁጥጥር ስር ነው ያለሁት፡፡ አባቴን ገደለ፡፡ አሁን ደግሞ ቀስ ብሎ እኔን ሊገድለኝ ነው›› ትላለች፡፡

‹‹ለዚህም ነው ለኔ እሱን ይቅር ማለት አማራጭ ያልነበረው፡፡››

ካንዲስ ሰውየውን ይቅር ማለት ትልቅ ነጻነት ሰጣት፡፡ ስሜቱ ልዩ ነበር፡፡ የይቅር ባይነት ስሜቱ የእውነት ሲሆን እጅግ ነጻ አወጣኝ፡፡ ገና ሰውየውን ሳላገኘው ራሴን መቆጣጠር ቻልኩ፤ መሳቅ መጫወትና የሆነውን መቀበል ጀመርኩ፡፡ ጤንነቴም ተመለሰ››

ልክ በ2014 የካንዲስ እናት ደብዳቤ ደረሳቸው፡፡ ከአቃቢ ሕግ ነበር ደብዳቤው፡፡ ቤተሰቡ በባሏ ግድያ ጉዳይ ከአጥፊው ጋር መነጋገር ከፈለጉ በአካል መገናኘት እንደሚችሉ ተነገራቸው፡፡

በሌላ ቋንቋ ነፍሰ በላውን ዩጂን ዲኮክን ፊት ለፊት በአካል የማግኘት እድል/እርግማን ማለት ነው፡፡

በዚህ ጊዜ ካንዲስ 23 ዓመቷ ነበር፡፡ እናትየው የደብዳቤውን ይዘት ነገሯት፡፡ መልሷ ፈጣን ነበር፡፡

‹‹በዚያ ቅጽበት ቶሎ እሺ ባልል ዕድሜ ዘመኔን እንደ እስረኛ በራሴው ስሜት ስሰቃይ እንደምኖር አውቀው ነበር›› ትላለች፡፡

የካንዲስ ማማ አባት በ21 ዓመቱ

የፎቶው ባለመብት, CANDICE MAMA

የአባትን ገዳይ ማቀፍ

የአባቷን ገዳይ ለማግኘት ቀጠሮ ተያዘ፡፡ ለባበሰች፡፡ ከእናቷ ጋር ተያይዘው ሄዱ፡፡ ነፍሰ ገዳዩን ዲኮክን የማገኝበት ክፍል ውስጥ ስገባ ከፍተኛ የስሜት መረባበሽ ተከሰተብኝ ትላለች፡፡

ነፍሰ በላው በሚል በመላው ደቡብ አፍሪካ የሚፈራው ሰው ቁጭ ብሏል፡፡ በቃ ሰው ነው፡፡ የ65 ዓመት ጎልማሳ ሰው፡፡ ሰይጣንን የመገናኘት ያህል ነበር የፈራቸው፡፡ ነገር ግን በቃ ኖርማል ሰው ቁጭ ብሏል፡፡ በፎቶ ላለፉት 20 ምናምን ዓመታት የምታውቀው፡፡ በሕልሟም በእውኗም እየመጣ የሚያሰቃያት ሰው፡፡ እንደ ማንኛውም ጤነኛ ሰው ቁጭ ብሏል፡፡

‹‹እርቁን የሚመሩት ቄስ ከእናቴ ባል ገዳይ፣ ከአባቴ ገዳይ አስተዋወቁኝ፡፡›

ይህ ነፍሰ ገዳይ እኔና እናቴን ሲጨብጥ፣ ስላገኘኋችሁ ደስ ብሎኛል ("Pleasure to meet you.") ይል ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ እናቷ በመጋቢት 26፣ 1992 በትክክል ባሏን እንዴት እንደገደለው እንዲነግራት ጠየቀችው፡፡

ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ዝርዝሩ ምን ይፈይዳል?

ተናግሮ ሲጨርስ ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ አልኩት፡፡

የፈለግሽውን አለኝ፡፡

ራስህን ግን ይቅር ትለዋለህ?

ዲኮክ ደነገጠ፡፡

‹‹እስከዛሬ ቤተሰባቸውን የገደልኩባቸውን ሰዎች ለማግኘት ስመጣ እንዳልጠየቅ የምፈረው አንድ ጥያቄ ቢኖር ይህንን ጥያቄ ነበር፡፡ በመጨረሻ አንቺ ጠየቅሽኝ›› ብሎ አቀረቀረ፡፡

ከዚያም ማንባት ጀመረ፡፡ ‹‹እኔ ቦታ ብትሆኚ ግን አንቺ ራስሽን ይቅር ትይው ነበር?›› ብሎ በጸጸት አነባ፡፡

ቄሱን ይቅርታ ጠይቄ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ የአባቴን ገዳይ አቀፍኩት፡፡ ተቃቅፈን አለቀስን፡፡ እስኪወጣልን ድረስ…፡፡