የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ንግግር ሥራ አስፈጻሚው አካል ላይ ተጽዕኖ ይፈጥር ይሆን?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እና አቶ ልደቱ አያሌው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በትናንትናው ዕለት በተካሄደው 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ፍርድ ቤቶች የሚሰጡትን ማንኛውም ውሳኔዎች አስፈጻሚው አካል ማክበር እንዳለበት አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት "እኛ ያላከበርነው እና ያልታዘዝነው ፍርድ ቤት ነጻና ገለልተኛ ሆነ ማለት ከንቱ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ለሕዝብ ተወካዮች ባብራሩበት ንግግራቸው የለውጥ ሀይሉ የፍትህ ስርአቱ ከፖለቲካ ጫና ነጻ እንዲወጣ ራሱን ችሎ እንዲፈርድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የምርጫ ቦርድ በአንድ እግራቸው እንዲቆሙ የሰራው ስራ ተስፋ ሰጪ ስለመሆኑም አንስተዋል።

ነገር ግን የፍትህ ስርአቱ ገለልተኛ ፤ነጻ ይሁን ያለው ይህ ኃይል የፍትህ ውሳኔዎችን የሚቃረን መሆን የለበትም በአስቸኳይ መታረም አለበት ብለዋል።

አሁንም ቢሆን ያልተፈቱ ድክመቶች እንዳሉ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፍርድ ቤቶች ለሚሰጧቸው ውሳኔዎችና ብያኔዎች ምንም ሳያወላዳ መቀበል ያስፈልጋል ብለዋል ፡፡

የአቶ ልደቱ ጠበቆች ከሆኑት መካከል አንዱ አቶ ገመቹ ጉተማ ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር የፈጠረባቸው ስሜት ምን እንደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ "ሀገር አይደለም አንድ ቤተሰብ ራሱ ለመተዳደር ሥርዓት ያስፈልገዋል" ብለዋል።

አቶ ገመቹ የአንድ አገር የሕግ በላይነት መገለጫ የፍርድ ቤት ነጻነት እና ትዕዛዝ ሲከበር መሆኑን ያነሳሉ።

የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሥራ አስፈጻሚው ተግባራዊ የማይደረግ ከሆነ የሕግ የበላይነት ችግር ውስጥ ይገባል የሚሉት ጠበቃ ገመቹ ሶስቱ የመንግሥት አካላት፣ ሕግ አውጪ ፣ ተርጓሚና አስፈጻሚ፣ አካላት አንዱ የሌላውን ትዕዛዝ የማያከብሩባት አገር ችግር ውስጥ ትገባለች ሲሉ ያክላሉ።

ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ በበኩላቸው ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር ተፈጻሚነት ይጠራጠራሉ።

ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ሲመጡ "ሳናጣራ አናስርም፣ በኔ የሥልጣን ዘመን አሳዳጅና ተሳዳጅ አይኖርም እንደሚለው ንግግራቸው ነው የወሰድኩት" ሲሉም ያክላሉ።

ጠበቃው አክለውም "ከሺህ ቃላት አንድ ተግባር ይበልጣል" በማለት ንግግራቸው በሌሎች የአስፈጻሚው አካላት ላይ ብዙም ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው ብለው እንደማያምኑ ይገልጻሉ።

ይህንንም በምሳሌ ሲያስረዱም የእርሳቸውን ንግግር ከተጠርጣሪዎች ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት አንስተውት እንደሚያውቁ በመግለጽ "ከምንም አይቆጥሩትም" ይላሉ።

የአቶ ልደቱን የፍርድ ቤት ውሎዎች በመጥቀስ "በተግባር ይህንን ነገር ቢፈጽሙት ደስ ይለኝ ነበር" ሲሉ ይናገራሉ።

ሄኖክ በበኩሉ በየዕለቱ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደማይከበር፣ ፍርድ ቤት እየተለማመጠ እንደሚገኝ በማንሳት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እንደ ሥራ አስፈጻሚነታቸው፣ በአዲስ አበባ፣ በፌደራል እንዲሁም በኦሮሚያ የሚገኙ የአስፈጻሚው አካላት ጋር ተሰብስበው መነጋገር እንደሚችሉ ይገልጻሉ።

አቶ ገመቹ በበኩላቸው የሥራ አስፈጻሚው ሶስቱ አካላት አንዳቸው ሌላኛቸውን የማይቆጣጠሩ ከሆነ (ቼክ ኤንድ ባላንስ)፣ የሚሰሩት ሥራ ዋጋ እንደሚያጣ ይናገራሉ።

"የሕግ አስከባሪው፣ በወንጀል ጠርጥሬዋለሁ ብሎ ቁጥጥር ስር አውሏል፤ እና ከመረመረ በኋላ ነው ወደ ፍርድ ቤት የሚያቀርበው፣ አቶ ልደቱ ወንጀሉን መጸፀሙን እና አለመፈፀሙን የሚያጣራው ፍርድ ቤቱ ነው፤ ግን ፖሊስ ራሱ ምርመራ አድርጎ ፍርድ ቤት ካደረሰው በኋላ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የማያስፈጽም ከሆነ ያ ምርመራ ዋጋ የለውም ማለት ነው" ይላሉ።

ፍርድ ቤትም የመንግሥት አካል ስለሆነ ትዕዛዙ መከበር አለበት የሚሉት ጠበቃው፣ የመንግሥት አካላትም መከባበር አለባቸው፣ የዛኔ ነው የሕግ የበላይነት የሚከበረው ሲሉ ያክላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በትናንትናው ንግግራቸው አሰፈጻሚው አካል ላይ ያለው ወንጀለኛን መደበቅ እና አልታዘዝም ማለት ፈጥኖ መታረም ያለበት ስለመሆኑም አንስተዋል።

ሄኖክ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካም ንግግሮች በበለጠ ተግባሩ ስለሆነ ጎልቶ የሚታየው፣ በተግባር ቢውል ሲሉ ሃሳባቸውን አጽንኦት ይሰጡታል።

"የፍትሕ ስርዓቱ በአጠቃላይ በተለይ ከፖለቲካ እስረኞች ጋር በተያያዘ ወደ ኋላ እየሄደ እንጂ ወደ ፊት እየተራመደ አይደለም" የሚሉት ጠበቃው አስፈጻሚው አካልን፣ መንግሥትን በአጠቃላይ፣ ተጠያቂ ለማድረግ መደረግ ካለባቸው ነገሮች መካከል አንዱ በማለትም

"አሁን የአቶ ልደቱን ጉዳይ ብንወስድ ፍርድ ቤቱ አስፈጻሚውን አካል ከመለማመጥ ለምንድን ነው የኦሮሚያ ፖሊስን የማያስረው፣ . . .ቢያስራቸው የተሻለ ለውጥ ይመጣል፣ እንደዚያ የሚቀልዱትን የፖሊስ ኃላፊዎች ደሞዛቸውን መቅጣት ይችላል፤ . . .ወደዚያ ተግባር ሲገባ አናይም። ነገር ግን ተከሳሹ እስር ቤት ይማቅቃል" በማለት ተጠያቂነትን ለመፍጠር ፍርድ ቤቶች በሕግ የተሰጣቸውን ስልጣን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ያነሳሉ።

በዚህች አገር ትልቅ ስልጣን ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደመሆናቸው የእርሳቸው ንገግር ሚዛን ይደፋል የሚሉት አቶ ገመቹ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚተላለፉ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችና ትዕዛዞች ስራ ላይ ባለማዋላቸው ይህ የጠ/ሚሩ ንግግር ለዚህ መፍትሔ ያመጣል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ይገልጻሉ።

የፌደራል የሥራ አስፈጻሚው አካል በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ስለሆነ፣ "ለወደፊት ይህ የእርሳቸውን ትዕዛዝ ተቀብሎ ወደ ተግባር ያውላል ብለን እንጠብቃለን" ሲሉም ተስፋቸውን ይገልጻሉ።