ዐብይ አሕመድ፡ ጠ/ሚር ዐብይ ከሕወሓት ጋር የተከሰተው አለመግባባት "በሕግ እና ሕግ ብቻ የሚመለስ ይሆናል" አሉ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ

የፎቶው ባለመብት, EBC

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ ተካሂዷል። በዚሁ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚንሰትሩ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።

ምጣኔ ሃብት

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ የ6.1 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት መመዝገቡን ይፋ አድርገዋል።

የኢንደስትሪ ዘረፉ ደግሞ ከፍተኛውን እድገት ካስመዘገቡ ዘርፎች መካከል ቀዳሚው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2012 የበጀት ዓመት 3.37 ትሪሊየን ብር ጠቅላላ አገራዊ ምርት መመዝገብ መቻሉንም ተናግረዋል።

የነፍስ ወከፍ ገቢም 1ሺህ ዶላር መድረሱን ተናግረው፤ ይህም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ኢትዮጵያን ማሰለፏን እንደሚያረጋግጥ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይፋ አድርገዋል።

በትግራይ እና በፌደራል መንግሥት መካከል ስላለው ግነኙነት

በትግራይ እና በፌደራል መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካረረ መጥቷል። ጠቅላይ ሚንስትር የትግራይ ሕዝብ በከፍተኛ ችግር እና ድህነት ውስጥ ያለ ሕዝብ ነው፤ "በሠላም እና ልማታዊ ሆኖ የመኖር መብት አለው። መለወጥ ይፈልጋል' ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከክልሉ ጋር የተከሰተው አለመግባባት "በሕግ እና ሕግ ብቻ የሚመለሰው ይሆናል" ያሉ ሲሆን የፌዴሬሽን እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጡት ውሳኔ ላይ ብቻ በመመሠረት ጉዳዩ በሕግ የሚመለስ መሆኑን ተናግረዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስለሚፈጸሙ ግድያዎች

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚከሰቱት ጥቃቶች ውስብስብ መሆናቸውን በሰጡት ምላሽ ወቅት አብራርተዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በክልሉ ያለው አለመረጋጋት ከሕዳሴ ግድብ ጋር እንደሚገናኝም ጠቁመዋል።

"ከሕዳሴ ጋር ይገናኛል። የሕዳሴን መንገድ መቁረጥ ጋር ይያያዛል" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ችግር በሚያጋጥምባቸው ስፍራዎች የመኪና መንገድ አለመኖሩንም ጨምረው ተናግረዋል።

በዚም ምክንያት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥቃት የተፈጸመበት ቦታ ለመድረስ እስከ 7 ሰዓት ድረስ በረዣዥም ሳር ውስጥ በእግራቸው እንደሚጓዙ አስረድተዋል።

"ጥቃቱ የሚፈጸመው በቀስት ነው። ሳቫና ግራስ ላንድ ውስጥ። ብዙ መስዋእትነት ተከፍሏል" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች መማረካቸውን እና ብዙዎቹ ጥቃት አድራሾች ደግሞ መሸሻቸውን ተናግረዋል።

"ችግሩ አሁንም ከምንጩ ካልደረቀ ችግር [ዳግም] ይከሰታል" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ መንግሥታቸው ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የገንዘብ ኖት ለውጥ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ባለፉት ሶስት ወራት መንግሥታቸው ካከናወነው ስኬታማ ሥራዎች መካከል የብር ኖት ለውጡ አንዱ መሆኑን አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የገንዝብ ለውጥ ውስጥ የነበረውን የሥራ ሂደት አስታውሰው በ31 ቻርተር አውሮፕላን አዲሱ የገንዘብ ኖት ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል። የሥራ ሂደቱም ከፍተኛ ጥንቃቄ እና በሚስጥር ተጠብቆ መቆየቱን አብራርተዋል።

አዲሱ የገንዘብ ኖት በ6ሺህ 628 የባንክ ቅርንጫፎች ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ መሰራጨቱን ተናግረዋል። 1.3 ሚሊዮን ሰዎች አዲስ የባንክ አካውንቶች መከፈታቸውን እና በእነዚህ የባንክ አካውንቶች 37 ቢሊዮን ብር ተቆጥቧል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህ ሥራ ሲሰራ የጎላ ችግር አንዳላገጠመ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የመቀየሪያ ጊዜ ማብቃቱን አስታውሰው አነስተኛ መጠን ያለውን የብር ኖት መቀየር ሥራ ይቀጥላል ብለዋል።

"እጅግ የተሳካ ሥራ ነው የተሰራው" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ለባንኮች እና የመንግሥት የጸጥታ አካላት እንዲሁም ብሔራዊ ባንክ እና የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ቡድን ለሠሩት ስኬታማ ሥራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ባንክ

በተያያዘ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በኢትዮጵያ የባንኮች ቁጥር መጨመሩን ተናግረው፤ የባንኮች መጨመር ቁጠባን ከፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ምንም እንኳን የባንኮች ቁጥር ከፍ ይበል እንጂ ዲጂታል ባንኪንግ የሚፈለገውን ያክል ለውጥ አለማምጣቱን ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ የባንኮችን የካፒታል አቅም ከፍ እንዲል እና ግዙፍ ባንኮች እንዲፈጠሩ ይሰራል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አነስተኛ እና ጥቃቅን የፋይንስ ተቋማት ወደ ባንክ ደረጃ ከፍ እንዲሉ መንግሥታቸው ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የዋጋ ግሽበት

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ መግሥታቸው ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቀው የዋጋ ግሽበት መጠኑን ዝቅ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።

"ሰፊ ሥራ የሚፈልገው የዋጋ ግሽበት ነው። ባለፉት ሶስት ወራት መቀነስ ያመላክታል። ግን ይህ በቂ አይደልም" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ። እንደማሳያም፤ ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቆጦች ላይ ባለፈው ሐምሌ የነበረው የዋጋ ግሽበት መጠን 22 በመቶ፣ ነሐሴ ወር 20 በመቶ እንዲሁም መስከረም ወር 18.7 በመቶ መሆኑን አመልክተዋል።

ባለፉት ሶስት ወራት ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቆጦች የተመዘገበው የግሽበት መጠን እየቀነስ ቢሆንም ይህ ግን በቂ አለመሆኑን አስምረውበታል።

በምግብ ምርቶች ላይም በተመሳሳይ ባለፉት ሶስት ወራት የዋጋ ግሽበት መጠኑን እየቀነሰ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል። ሐምሌ ወር 24.9 በመቶ፣ ነሐሴ ወር 22 በመቶ እንዲሁም መስከረም ላይ ደግሞ 21 በመቶ መሆኑን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የዋጋ ግሽበቱን መጠን ለመቀነስ በቅድሚያ ለዋጋ ግሽበቱ ገፊ ምክንያቶች ምንድናቸው የሚለውን መለየት ያስፈልጋል ብለዋል። የግብርና ምርት ውጤቶችን ማሳደግ ደግሞ ሌላው የዋጋ ግሽበቱ መጠን ለመቆጣጠር ሌላኛው መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል።

ሉዓላዊ አገር

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ኢትዮጵያ የትኛውንም አይነት ጥቃት የመከላከል አቅም እንዳለት ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

"መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ የትኛውንም ጥቃት የመከላከል አቋም ላይ ይገኛሉ" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።

ፍትሕ

የፍትህ ስርዓቱ ነጻ እና ገለልተኛ መሆን አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ሰኔ 16፣ ሰኔ 15 እና ሰኔ 23 የተያዙ ጉዳዮች የደረሱበትን ደረጃ አብራርተዋል።

በጠቅላይ ሚንስትሩ ድጋፍ በተጠራው ሰልፍ ላይ ለተደረው "የግድያ ሙከራ" ወንጀል ክስ በተመሰረተባቸው ግለሰቦች ላይ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን በሙሉ መስማታቸውን ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል። ተከሳሾችም መከላከያዎቻቸውን ማቅረባቸውን ተናግረው በቅርቡ ብይን ይሰጣል ተብሎ እንደሚተበቅ ተናግረዋል።

ሰኔ 15 በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል በከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ላይ የተፈጸውን ግድያ ተከትሎ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች የክስ ሂደት የደረሰበትን ደረጃም ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ በቁጥጥር ሥር በዋሉት ተከሳሾች ዙሪያ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ሙሉ ለሙሉ መሰማታቸውን ተከሳሾችም መከላከያዎቻቸውን እያሰሙ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል። በአማራ ክልል ለተከሰተው ወንጀልንም በተመለከተ ሲናገሩ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቹን እያሰማ ይገኛል ብለዋል።

ሰኔ 23 ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከት ጋር በተያያዘ 114 የክስ መዝገቦች መከፈታቸውን ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ተናግረው፣ በመዝገቦቹ ላይ የወንጀል ክስ መመሠረት ስራ ከሞላ ጎደል ተከናውኗል ብለዋል።

ይሁን እንጂ የዳኛ እጥረት እና የኮሮናቫይረስ ስርጭት በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ፈተና ሆኖ እንደነበረ ተናግረዋል።

የእዳ መጠን

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በአገሪቱ የሚገኙ ግዙፍ ኩባንያዎች ከ600 ቢሊዮን ብር በላይ እዳ ተከማችቶባቸው እንደነበረ ተናግተዋል።

እነዚህ ኩባንያዎች ከአገሪቱ በጀት በላይ እዳ ውስጥ ተዘፍቀው እንደነበረ ተናግረው እነዚህን ኩባንያዎች መልሰው እንዲዋቀሩ በመደረጉ ተጋርጦባቸው ከነበረው አደጋ መንግሥት እንደታደጋቸው ተናግረዋል።

መልሶ የዋቃሩ ስራ ባይሰራ ኖሮ "ስለመብረት እና ስኳር ማውራት አንችልም ነበር" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ።

ሲሚንቶ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በአገሪቱ የሲሚንቶ እጥረት ተከስቶ እንደነበረ አስታውሰው፤ በአሁኑ ሰዓት 10 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች 14 ሚሊዮን ቶን በየዓመቱ የማምረት አቅም ቢኖራቸውን እየተመረተ ያለው ግን 8 ሚሊዮን ቶን ብቻ ነው ብለዋል።

በዚህም ምክንያት የሲሚንቶ ዋጋው ከፍ ብሎ እንደነበረ አስታውሰው፤ የሲሚንቶ ምርትን ለመጨመር ከፋብሪካዎቹ ጋር ውይይቶች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ሲሚንቶ አምራቾች የውጪ ሚንዛሬ እና የኃይል አቅርቦት ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ለመስጠት ሞክሯል፤ በዚህም የምርት መጠን ላይ ለውጥ ታይቷል ብለዋል።

"በአሁኑ ሰዓት በአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ላይ የ60 ብር ቅናሽ ታይቷል" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት

ለውጥ ለማምጣት በትኩረት ሊሰራባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ ኤሌክትሪክ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ባለፉት ሶስት ወራት 69 ከተሞች መብራት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል። የሕዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተም፤ "ጥሩ ሥራ ሰርተናል። የዘንድሮ ሥራ ግን ፈታኝ ይሆናል" ብለዋል።

የሕዳሴ ግድብ የዘንድሮ የኤልክትሮ መካኒካል እና የሲቪል ሥራው ፈታኝ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚንሰትሩ ጠቁመው፤ "ሥራው ከውስጥም ከውጪም እንዲደናቀፍ የሚፈልጉ አሉ" ካሉ በኋላ በተባበረ መንፈስ በሙሉ ልብ የሕዳሴ ግድብ ላይ ትኩርት መደረግ አለበት ብለዋል።

መፈናቀል

የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በከፍተኛ መጠን የቀነሰ ቢሆንም አሁንም በሚከሰቱ ግጭቶች ሰዎች ከቀያቸው እየተፈናቀሉ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ አስታውሰዋል።

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወደ 56ሺህ ያህል ሰዎች መፈናቀላቸውን ተናግረው፤ ከእነዚህ መካከል ወደ 50ሺህ የሚጠጉት ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

አሁንም የአገር ውስጥ መፈናቀል እንዲከሰት በሚያደርጉ መንስኤዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

አንበጣ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የአንበጣ መንጋው ጥቃት ያደረሰው በ240 ወረዳዎች መሆኑን ገልጸዋል።

በቅርቡም ከሌሎች አገራት መሪዎች ጋር በነበሯቸው ውይይቶች አንዱ አጀንዳ የአንበጣ መንጋ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከውጪ ኬሚካል የሚረጩ አውሮፕላኖችን እና ድሮኖችን [ሰው አልባ አውሮፕላን] ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ሂደቱ ግን አልጋ ባልጋ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ አመልክተዋል።