የሕዳሴ ግድብ፡ "በግድቡ ዙሪያ የሚሰጡ ማስፈራሪያዎች ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሱ ናቸው"

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

የፎቶው ባለመብት, Simona Granati - Corbis

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በግድቡ ዙሪያ የሚሰጡ ማስፈራሪያዎች ከመረጃ ክፍተት የሚነሱ፣ ውጤታማ ያልሆኑ እና የዓለም አቀፍ ሕግን የጣሱ ናቸው አለ።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ ጽህፈት ቤት የትናንት ማታውን የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተያየት ተከትሎ ማለዳውን ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ኢትዮጵያ ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን የናይል ውሃ ፍትሃዊ ክፍፍል ላይ ያላትን ቁርጠኝነት መግለጿን አመልክቷል።

የጽህፈት ቤቱ መግለጫ እንዳመለከተው፣ ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ወዳልሆነ ስምምነት ውስጥ እንድትገባ "የሚሰጡ ጠብ አጫሪ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም" ብሏል።

በተጨማሪም "ኢትዮጵያ ለማንኛውም ማስፈራሪያ አትንበረከከም እንዲሁም በቅኝ ግዛት ለተመሰረተ ውልም እውቅና አትሰጥም" በማለት አስፍሯል።

ትራምፕ በትናንትናው ዕለት ሱዳንና እስራኤል ግንኙነታቸውን ለማደስ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ በጽህፈት ቤታቸው ጋዜተኞች በተሰበሰቡበት ለሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ደውለው ባነጋገረወቸው ወቅት ኢትዮጵያ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ስምምነትን ጥላ መውጣት አልነበረባትም ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

የቀጥታ የስልከ ውይይቱ ሲካሄድ ጋዜጠኞች ተገኝተው የነበረ ሲሆን የሱዳኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ግድቡን በሚመለከት በቅርቡ በሶስቱ አገራት መካከል ስምምነት ይደረሳል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር "በቅርቡ ስምምነት ላይ እንደርሳለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ያሉ ሲሆን ጋዜጠኞች በተሰበሰቡበት ሁለቱን መሪዎች የሚያናግሩት ትራምፕ ግን፣ ለግብጽም ተመሳሳይ ነገር መናገራቸውን በመጥቀስ ሁኔታው አደገኛ መሆኑን ገልፀው፣ ግብጽ "ግድቡን ታፈነዳዋለች" ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፉ አስተያየቶች ከመረጃ ክፍተት የሚነሱ፣ ፍሬ አልባ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ሕግን የጣሱ መሆናቸውን በመግለጫው ላይ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር ቁርጠኛ መሆናቸውን የገለፀው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት መግለጫ ኢትዮጵያ በየትኛውም "ጠብ አጫሪነት ውስጥ" ግን እንደማትሳተፍ አስታውቋል።

አክሎም ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ወቅት ለተደረጉ ስምምነቶችም ተገዢ እንደማትሆን እንዲሁም መብቷንም አሳልፋ እንደማትሰጥ መግለጫው አትቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በዚህ መግለጫው በግድቡ ዙሪያ የሚካሄዱ ድርድሮችን ላይ አሁንም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ገልጿል።

በኋይት ሐውስ የሆነው ምን ነበር?

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት (አርብ) ምሽት በዋይት ሃውስ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ ኢትዮጵያ ወደ ስምምነቱ መመለስ አለባት፤ ግብጽ ብስጭት ቢገባት ልትኮነን አይገባም፤ "ያን ግድብ ልታፈነዳው ትችላለች" ሲሉ ተደምጠዋል።

ትራምፕ ኢትዮጵያ ጥላ ወጣች ያሉት ስምምነት የትኛው ስለመሆኑ ያሉት ነገር የለም።

ሱዳን እና እስራኤል የሰላም ስምምነት መድረሳቸውን በማስመልከት ዛሬ በዋይት ሃውስ ትራምፕ የሁለቱን አገራት መሪዎች ጋዜጠኞች በተገኙበት በስልክ ሲያነጋግሩ ነበር።

ፕሬዝደንት ትራምፕ የሱዳኑን ጠቅላይ ሚንስትርን፤ "በመስመሩ ላይ እያሉ ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ እንዴት እየሆነ ነው?" በማለት የጠየቁ ሲሆን ግድቡ ውሃ ወደ ታችኛው የተፋሰስ አገራት እንዳይፈስ መከልከሉን ሲናገሩ ይደመጣል።

አክለውም ከግብጽ እና ኢትዮጵያ ጋር ሶስተኛ ወገን ሆናችሁ ጉዳዩን በቅርብት እየተመለከታችሁ ነው። ከምን ደረሰ? ሲሉ ጠይቀዋል።

ትራምፕ ለሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ሳይጠብቁ፤ "ስምምነት እንዲደርሱ አድርጌ ነበር። ኢትዮጵያ ግን ስምምነቱን ጥላ ወጣች። ያን ግን ማድረግ አልነበረባቸውም። ትልቅ ስህተት ነው የሰሩት። በዚህም ብዙ እርዳታ አቋርጠንባቸዋል። ለስምምነቱ ተገዢ እስካልሆኑ ድረስ ያን ገንዘብ መቼም አያገኙትም። ውሃ ወደ ናይል ወንዝ እንዳይፈስ የሚያቆም ግድብ ገነቡ፤ ግብጽ በዚህ ብትበሳጭ መኮነን የለባትም። እንዴት እየሆነ ነው? ምን ያውቃሉ?" ሲሉ ለሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር በድጋሚ ጥያቄ አቅርበዋል።

በዚህ መካከል በስልክ መስመር ላይ የሚገኙት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ጣልቃ ሲገቡ፤ ትራምፕ ጥያቄውን ለሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር ያቀረቡት መሆኑን ተናግረዋል።

ትራምፕ "ለዚህ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚፈልግ [የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር] አይመስለኝም" ካሉ በኋላ ፈገግ ብለዋል።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር፤ "ሁሉንም ሊጠቅም የሚችል ሁሉን አካታች ስምምነት በቅርቡ እንደርሳለን ብለን እናስባለን" በማለት የመለሱ ሲሆን ትራምፕ ተቀብለው፤ "እንደዛ ሊሆን አይችልም ምክንያቱም ስምምቱን አፍርሰዋል። ይህን ደግሞ ከፍተኛ አጣብቂኝ ፈጥሯል። ግብጽ በዚህ ሁኔታ መኖር አትችልም። ልታፈነዳው [ግብጽ] ትችላለች። ደግሜ እናገራለሁ ግብጽ ግድቡን ታፈነዳዋለች" ሲሉ ተደምጠዋል።