Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያውያን የፕሬዚዳንት ትራምፕን አስተያየት በመቃወም በዋሽንግተን ዲሲና በለንደን ሰልፍ አካሄዱ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን አስተያየት በመቃወም ኢትዮጵያውያን በለንደን እና በዋሽንግተን ዲሲ የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ።

በአሜሪካዋ ዋሽንግተን ዲሲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሰጡትን አስተያየት በመቃወም ከፕሬዚዳንቱ መኖሪያ ስፍራ “ኋይት ኃውስ ” ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተያየት የሁለቱን ሀገራት የቆየ ወዳጅነት የሚያሻክር እና ተገቢነት የሌለው ነው ሲሉም ተችተዋል።

በለንደን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም የፕሬዚዳንት ትራምፕን አስተያየት በመቃወም ለንደን በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰልፍ አካሄደዋል።

በፕሬዚዳንቱ አስተያየት የተበሳጩ ኢትዮጵያውያን ትናንት “የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኔ ነው!”፣ “አሜሪካ ገለልተኛ አይደለችም” የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ሰልፍ ወጥተዋል።

ሰልፈኞቹ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለግዴለሽ አስተያየታቸው ይቅርታ መጠየቅ ይኖርባቸዋልም ብለዋል።

“በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በቅርቡ የሰጡትን አስተያየት እንዲያስተባብሉ እና ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ ለማቋረጥ የወሰኑትን ውሳኔ ዳግም እንዲያጤኑት እንጠይቃለንም” ይላል በብሪታንያ የኢትዮጵያውን ማህበር ያወጣው መግለጫ።

ምንጭ፦ ቪ.ኦ.ኤ እና ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.