ሰሜን ኮሪያ ከቻይና ይመጣል ባለችው "ቢጫ አቧራ ምክንያት" ማስጠንቀቂያ አስተላለፈች

የሰሜን ኮሪያ ቴሌቪዥን ስክሪን ግራብ

የፎቶው ባለመብት, KCTV

ሰሜን ኮሪያ ከቻይና የሚመጣ ቢጫ አቧራ ምክንያት ዜጎቿን ከቤት አትውጡ ስትል አስጠንቅቃለች። ይህ የሰሜን ኮርያ መንግሥትን ያሰጋው "ቢጫ አቧራ" ከቻይና ስለሚነፍስ ኮሮናቫይረስ ሊያመጣብን ይችላል በሚል ነው።

ቢጫ አቧራ ከሞንጎሊያና ቻይና በረሃማ አካባቢዎች የሚነሳ አሸዋ ያዘለ አቧራ ሲሆን በሰሜን እና ደቡቡ ኮሪያ ይነፍሳል።

የፒዮንግ ያንገግ ዋና አውራ ጎዳናዎች፣ ከሐሙስ እለት ጀምሮ ጭር ማለታቸው ተዘግቧል።

ሰሜን ኮሪያ ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆኗን ብትናገርም ከታሕሳስ ወር ጀምሮ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላ ድንበሮቿን ዘጋግታ በከፍተኛ ጥንቃቄ ላይ ትገኛለች።

እስካሁን ድረስ በወቅታዊ አሸዋ አዘል አቧራ እና በኮቪድ-19 መካከል ስላለ ግንኙነት ምንም የሚታወቅ ነገር የለም።

ይሁን እንጂ ሰሜን ኮሪያ ብቻ አይደለችም ይህንን ጥቅጥቅ አቧራ ከኮሮናቫይረስ ጋር በማያያዝ ስትናገር የተደመጠችው።

ከዚህ ቀደም ቱርኬሚስታን ዜጎቿን የአፍና አፍንጫ ጭምብል እንዲያደርጉ ያዘዘችው ይህንን ጥቅጥቅ አቧራማ ደመና ኮሮናቫይረስ ያስከትላል ስትል በመናገር ነበር።

በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኘው የኮሪያ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣብያ፣ ኬሲቲቪ ረቡዕ እለት የአየር ትንበያ መረጃ የያዘ ልዩ ፕሮግራም አስተላልፎ ነበር።

በዚህ ፕሮግራሙ ላይ በሚቀጥሉት ቀናት ቢጫ የአቧራ ደመና እንደሚመጣ በመግለጽ አስጠንቋቋል።

በተጨማሪም ከቤት ውጪ የሚደረጉ ግንባታዎች በሙሉ ታግደዋል።

ይህ አቧራ የሁለቱ አገራት ዜጎችን መርዛማ አቧራ ነው በሚል የጤና ስጋት ሲጥል የቆየ ነው፥።

ሐሙስ እለት ለመንግሥት ወገንተኛ የሆነው ሮዶንግ ሺንሙን የተሰኘው ጋዜጣ " ሁሉም ሰራተኞች. . . ቫይረሱን አደገኛነት ሊገነዘቡ ይገባል" ብሏል።

በሰሜን ኮሪያ የሚገኙ ኤምባሲዎችም የፒዮንግያንግ አቧራ ስጋት በሚመለከት መረጃ ደርሷቸዋል።

በፒዮንግያንግ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በፌስቡክ ገጹ ላይ ከሰሜን ኮሪያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በአገሪቱ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖችን እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ስለ አቧራው ማስጠንቀቂያ እንደደረሳቸው እና በቤት ውስጥ እንዲቆዩ፣ መስኮታቸውን አጥብቀው እንዲዘጉ ማስጠንቀቁን አስፍሯል።

የሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን ኮሮናቫይረስ ላይ የሚደረጉ ምርምሮች ቫይረሱ አየር ወለድ መሆኑን በመግለጻቸው "የሚመጣው የቢጫ አቧራ ስርጭቱን እንዳያስፋፋ በጥብቅ ክትትል እናደርጋለን" ሲል ገልጿል።

የአሜሪካው በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ድርጅት ኮሮናቫይረስ በአየር ላይ "ለሰዓታት ይቆያል" ቢልም ሰዎች በዚህ መንገድ በቫይረሱ የመያዝ እድላቸው በጣም አነስተኛ ነው ሲል አስታውቋል።

የደቡብ ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን ከቻይና የሚነሳው ቢጫ አቧራ ኮሮናቫይረስ ሊያስከትል ይችላል የሚለውን ስጋት መሰረተ ቢስ ሲል አጣጥሎታል።