አሜሪካ፡ በካሊፎርኒያ ጥቃት ጥቅም ላይ የዋሉትን መሳሪያዎች የገዛው አሜሪካዊ ተፈረደበት

በሳን በርናርዲኖ ጥቃት የተጎዳ መኪና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እኤአ በ2015 በካሊፎርኒያ ጥቃት ለፈፀሙ ጥንዶች መሳሪያ ገዝቶ የሰጠው አሜሪካዊ 20 ዓመት እስር ተፈረደበት።

ኤኒሪኬ ማርኬዝ ጁኒየር የ29 ዓመት ወጣት ሲሆን ለሲያድ ሪዝዋን ፋሩክ እና ታሽፌን ማሊክ የጦር መሳሪያ በማቅረብ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ግለሰቦቹ በሳን በርናርዲኖ የገና በዓልን ለማክበር የተሰባሰቡ ሰዎች ላይ በመተኮስ ጥቃት ፈጽመዋል።

በጥቃቱ 14 ሰዎች ሲሞቱ 22 ሰዎች ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። ከፖሊስ ጋር በነበረው የተኩስ ልውውጥም ፋሩክ እና ማሊክ ተገድለዋል።

ማርኬዝ በፋሩክ አማካኝነት ወደ አክራሪ ሙስሊምነት መቀየሩን የሚናገሩት የአሜሪካ ባለስልጣናት በ2011 እና በ2012 መሳሪያዎችን ገዝቶ ነበር።

በወቅቱ መሳሪያውን ሲገዛ ለግሉ ለመጠቀም መሆኑን በሞላው ቅጽ ላይ አስፍሯል።

አቃቤ ሕጎች ማርኬዝ መሳሪያዎቹ ስለምን አገልግሎት ሊውሉ እንደሚችሉ በቂ ግንዛቤና እውቀት ነበረው ሲሉ ተከራክረዋል።

አቃቤ ሕግ አክሎም ከሳን በርናርዲኖ ጥቃት ዓመታት በፊት ማርኬዝና ፋሩክ በአንድ የማህበረሰብ ኮሌጅና በዋና አውራ መንገድ ላይ ጥቃት ለመፈፀም አቅደው ነበር።

ነገር ግን ማርኬዝ በካሊፎርንያ ውስጥ ሶስት ሰዎች የአሜሪካ ወታደሮችን ለመግደል ወደ አፍጋኒስታን ለመሄድ በማቀዳቸው ምክንያት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሲሰማ እቅዱን ሳይቀበለው ቀርቶ ከፋሩክ መራቁ ተገልጿል።

ለጥቃቱ የተጠቀሙበት መሳሪያ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የማርኬዝ ተከላካይ ጠበቃ ፋሩክ ደንበኛቸውን ጎረቤታሞች ሆነው ከተገናኙበት ከ13 ዓመቱ ጀምሮ አእምሮውን በመጠምዘዝ እንደቀየረው በመግለጽ ተከራክረዋል።

አክለውም ማርኬዝ መሳሪያዎቹ ለምን ጥቅም እንደሚውሉ እንደማያውቅ አስረድተዋል።

በ2017 ማርኬዝ ለአሸባሪዎች የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ እና በፋሩክ ገንዘብ የገዛቸውን መሳሪያዎች በሚመለከት ሀሰተኛ መረጃ በመስጠት ጥፋተኛ ተብሏል።