በትግራይ እና በፌደራል መንግሥት መካከል ያለውን ፍጥጫ ለመፍታት ምን መደረግ አለበት?

(ከግራ ወደ ቀኝ) ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ አቶ አሉላ ሃይሉ፣ አቶ አዳነ ታደሰ፣ አቶ ናትናኤል ፈለቀ

የፎቶው ባለመብት, BBC/WOYIN/EDP/ECSJ

የምስሉ መግለጫ,

(ከግራ ወደ ቀኝ) ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ አቶ አሉላ ሃይሉ፣ አቶ አዳነ ታደሰ፣ አቶ ናትናኤል ፈለቀ

በትግራይ ክልልና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ያለው ግነኙነት ከጊዜ ወደጊዜ እየሻከረ መጥቷል።

በሁለቱ አካላት መካከል ያለው አለመግባባትም አንዳቸው ሌላኛቸውን "ሕገ ወጥ" እስከ ማለት ያደረሰ እና የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውንም ማቋረጣቸውን በይፋ እስከ መግለጽ አድርሷቸዋል።

ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት ሲራዘም፣ የትግራይ ክልል የራሱን ክልላዊ ምርጫ ማካሄዱ ይታወሳል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ምርጫው ከመከናወኔ በፊት ምርጫው ቢካሄድም ሕገ-ወጥ ነው ሲል ቆይቶ፣ ምርጫው ተደርጎ ውጤቱ ይፋ ከሆነ በኋላ ደግሞ ምርጫው እንዳልተደረገ የሚቆጠርና ተፈጻሚነት የማይኖረው ይሆናል ሲል አስታውቋል።

በዚህ ብቻ ሳያበቃም የፌደራል መንግሥት የትግራይ ክልል ሕዝብ የልማትና መሠረታዊ አገልግሎቶች ፍላጎት ላይ በማተኮር የከተማ እና የቀበሌ አስተዳደርን ጨምሮ በክልሉ ከሚገኙ ሕጋዊ ተቋማት ጋር ብቻ ግንኙነት እንዲያደረግ ወስኗል።

የትግራይ ክልል በበኩሉ ውሳኔውን ቅቡልነት የሌለው በማለት ምክር ቤቱ ሥልጣኑን ከሕገ መንግሥቱ ውጪ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም በመስጠት ያራዘመ ስለሆነ፤ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የለውም ብሏል።

ይህ የሁለቱ አካላት ፍጥጫ እንዴት ይፈታ? የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናስ ምን መሆን አለበት ስንል የተለያዩ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግረናል።

ውይይት ውይይት ውይይት

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና "አደገኛ ወደ ሆነ ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል" በማለት ሁሉም አካላት ከገቡበት አለመግባባት ተመልሰው ወደ ድርድር እንዲገቡ እንደሚጠብቁ ይናገራሉ።

የፖለቲካ ልዩነቶች በድርድር መፈታት አለባቸው የሚሉት ፕሮፌሰሩ የትግራይ ክልል መንግሥትን እና የፌደራል መንግሥቱን ፍጥጫ ለመፍታትም "መፍትሔው ድርድር ብቻ ነው" ይላሉ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ሕወሓትና የፌደራል መንግሥቱ የገቡት እሰጥ አገባ "አደጋ ይጋርጣል" ሲሉ ከፕሮፌሰር መረራ ሃሳብ ጋር ይስማማሉ።

አክለውም በኢትዮጵያ ውስጥ የለውጥ ሂደቱ ተጀመረ ከተባለበት ጊዜ አንስቶ ሕወሓት በበላይነት ያስተዳድረው ከነበረው የፌደራል መንግሥት መገለሉን፤ በኋላም ላይ ብልጽግና ሲመሰረት ከፌደራል ሚና ወጥቶ ክልሉን ብቻ ወደ ማስተዳደር መቀየሩን አስታውሰው፤ በጊዜ ሂደት ሕወሓት እየወሰዳቸው የመጣቸው ውሳኔዎች ራሱን የሚነጥልና ከአገራዊ የለውጥ ሂደቱ ራሱን የሚያስወጣ ሂደት ተከትሏል ይላሉ።

የኢዜማው አቶ ናትናኤል፣ የፌደራል መንግሥቱንና የትግራይ ክልልን የሚያስተዳድሩት አካላት ያላቸው አለመግባባት የትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ አደጋ ሊጋርጥ የሚችል ይመስላል በማለት፣ ጉዳዩን "በውይይት ለመፍታት የሚያስችሉ በሮች እየተዘጉ ከዚያ ውጪ ያሉ አማራጮችን ለማየት የሚያስገድዱ ይመስላሉ" ሲል ይገለፁታል።

የፌደራል መንግሥቱን ከማንም በላይ ሊያሳስበው የሚገባው ሕግ የማስከበር፣ የዜጎችን ደህንንት የማስከበር ነው በማለትም ጉዳዩ ከዚህ በላይ ሳይባባስ ወደ ውይይት ሁለቱ ወገኖች የሚመጡበትን ሁኔታ የማመቻቸት የበለጠ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ይገልጻሉ።

ኢዜማም የፌደራል መንግሥቱ ያንን ማድረግ አለበት ሲል አንደሚያምን የገለፁት አቶ ናትናኤል፤ የሚወሰዱ እርምጃዎች በሙሉ ሕወሓትን ወደ ጠረጴዛ እንዲመጣ የሚጋብዙ አለበለዚያም የሚያስገድዱ መሆን አለባቸው ይላሉ።

የፌደራል መንግሥቱ የሚወስዳቸው እርምጃዎች የትግራይን ሕዝብ ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚጥል መሆን እንደሌለበትም አቶ ናትናኤል ጨምረው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሰ በበኩላቸው በአገሪቱ ውስጥ የተለያዩ የፖለቲካ ችግሮች ቢኖሩም አገሪቱ ሕልውና ላይ ተጨባጭ አደጋ ጋርጦ ያለው በሕወሓት እና በብልጽግና፣ በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል መንግሥት መካከል ያለው ፍጥጫ ነው ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።

ፓርቲያቸው ከባለፈው ዓመት ጥር ወር ጀምሮ ይህንን በመገንዘብ አቋሙን ሲገልጽ እንደነበር በማስታወስም፣ ሁለቱን ወገኖች ለማቀራረብ በሚደረግ ማንኛውም ተሳትፎ ውስጥ የፓርቲያቸው ሚና የሚያስፈልግ ከሆነ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑንም ማስታወቁን ይገልጻሉ።

ከፌደራል መንግሥት ወገን ክልሉን "የመግፋት"፤ ከትግራይ ክልል ወገን ደግሞ "ሆን ተብሎ ችግሮቹን የማስፋት አዝማሚያ" የሚታይ መሆኑንም በመጥቀስ ይህ ለአገር ትልቅ ስጋት መሆኑን ይገልጻሉ።

አቶ ታደሰ ሁለቱ አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀራርበው ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ አለባቸው ሲሉ ይገልጻሉ።

ኃላፊነት ያለባቸው የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችም ቢሆኑ የችግሩን አደገኛነት ተረድተው ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ያስታውሳሉ።

6ኛው ሃገራዊ ምርጫ መራዘሙ ትክክል እንዳልሆነና ትግራይ ክልላዊ ምርጫ በማካሄድ መንግስት ማቋቋም መቻሏ ህጋዊነት እንዳለው የሚገልጸው የሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት) ምክትል ሊቀመንበር አቶ አሉላ ሃይሉ በብልጽግናና ህወሓት መካከል ያለው "አደገኛ አለመግባባት" ግን በአስቸኳይ መፈታት እንዳለበት ያምናል።

ፓርቲዎቹ ችግራቸውን በራሳቸው መንገድ መፍታት እንዳለባቸው የሚናገረው አሉላ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ግን በህጋዊ መንገድ መፈታት እንደሚኖርበት የፓርቲያቸው ሳወት አቋም መሆኑን ይገልጻ።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እና የሕወሓት አቋም

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሕገመንግሥት አጣሪ ጉባኤ የቀረበለትን ውሳኔ በመንተራስ አገራዊ ምርጫውንም ሆነ የመንግሥትን ስልጣን ለማራዘም መወሰኑ ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም ምክር ቤቱ የትግራይ ክልል መንግሥት ያካሄደው ምርጫ ተፈጻሚነት የሌለው፣ የማይጸና እና እንደተደረገ የማይቆጠር በማለት፣ ከክልሉ መንግሥት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደማይኖር በማስታወቅ፣ ከታችኛው መዋቅሮች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሚደረግ ወስኗል።

ሕውሃትም ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቋል።

ይህንን በማስመልከትም የኦፌኮው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ፤ የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልል መንግሥት አንዳቸው አንዳቸውን በመወንጀልና "ሕገ-ወጥ" በማለት ግንኙነት ማቋረጣቸው ተገቢ አለመሆኑን ይገልጻሉ።

የፌደራል መንግሥት ከወረዳና ቀበሌ አስተዳደሮች ጋር ግንኙነቱን አደርጋለሁ ማለቱ በምን መልኩ ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ለፕሮፌሰሩ መመለስ ያለበት ነጥብ ነው።

በእርሳቸው እምነት በበላይነት ክልሉን የሚያስተዳድረው አካል የታችኛው መዋቅሩንም የማደራጀት ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ፣ የፌደራል መንግሥቱ፣ ሕወሓትን አልፎ ከታችኛው መዋቅር ጋር ምን ምን እንደሚሰራ መታወቅ እንዳለበት በማንሳት፣ ወደ ስራ ለመተርጎምም ቀላል ይሆናል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልፀዋል።

ሕዝቡን የሚያስተዳድር እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን የሚያሟላው አካል የተለያዩ መሆናቸው ለአፈጻጸም አስቸጋሪ እንደሚያደርገውም ያነሳሉ።

ፕሮፌሰር መረራ አክለውም እነዚህ ሁለት አካላት ዋነኛ የፖለቲካ ችግራቸውን እስካልፈቱ ድረስ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ አብሮ መጓዝ እንደሚከብዳቸውንም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት የሆኑት አቶ ናትናኤል በበኩላቸው ሕወሓት ቀደም ብሎ ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም የሚል ቅስቀሳ እና ንግግሮች በተደጋጋሚ ሲያደርግ እንደነር በማስታወስ፣ ቅስቀሳውም ሆነ ውሳኔው "አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚከተን ነው የሚሆነው" ብለዋል።

"ይህ አደገኛ ቅስቀሳ እንደ አገር አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንደሚከተን አድርገን ነው ያየነው" የሚሉት የኢዜማው አቶ ናትናኤል የፌዴሩሽን ምክር ቤቱ ከትግራይ የክልል መንግሥት በታች ካሉ መዋቅሮች ጋር ግንኙነት ለማድረግ መወሰኑ አግባብነት ያለው ነው ብለን ነው የምንወስደው ብለዋል።

ውሳኔው ግን ምን ያህል ሁለቱን ወገኖች የሚያቀራርብና ወደ ውይይት ያመጣል የሚለው ላይ አሁንም ስጋት እንዳላቸው ከመግለጽ አልተቆጠቡም።

ስለዚህ ሕወሓትን ወደ ውይይት ጠረጴዛ ለማምጣት ምን መደረግ አለበት የሚለው በሚገባ መታሰብ እንዳለበት ይገልጻሉ።

የኢዴፓው አቶ አዳነ በበኩላቸው ሕወሓት ምርጫ አድርጎ ስልጣኑን ያራዘመበት መንገድ ፍፁም ተገቢ ያልሆነ እና ሕገ-መንግስታዊ ነው ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ የፌደራል መንግሥቱም ሥልጣኑን ያራዘመበት መንገድም ሕገ ወጥና ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ መሆኑን ይገልጻሉ።

ከዚህ አንጻር በፌደሬሽን ምክር ቤት እና በትግራይ ክልል መካከል የሚካሄዱ ሕጋዊ የሚመስሉ ምልልሶች ተገቢ አለመሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

ከዚህ ይልቅ "ሕጉን ወደ ጎን ትቶ፣ በዚያ ሰበብ ሕዝብ ማደናገሩን ትቶ፣ ፖለቲካዊ መፍትሄ መስጠት" እንደሚያሻቸው ይናገራሉ።

ብልጽግናና ሕወሓት በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው ችግሮቻቸውን መፍታት አለባቸው በማለትም፣ "እነርሱ በያዙት የፖለቲካ ጨዋታ አገር ይፈርሳል" በማለት ፖለቲካዊ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ድርድርና ውይይት ማድረግ እነደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚና

የሳወት ሊቀመንበር አቶ አሉላ ሃይሉ እንደሚለው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብልጽግናን እና ህወሓትን በማስታረቅ የሚፈለገውን መግባባት ለመፍጠር የሚያስችላቸው ዕድል ሊኖር አይችልም።

"የነበረው የኢህወዴግ ስርዓት በወቅቱ ሲፈጠሩ የነበሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደካማ እንዲሆኑ ያደርግ ነበር። አንዳንድ ጠንካራ የሚባሉ ከተፈጠሩም በገዢው ግንባር የሚታፈኑበት ሁኔታ ነው የነበረው። ስለዚህ አሁንም የመሰማት ወይም የመደመጥ ዕድል ያገኛሉ ብዬ አላስብም" በማለት ምክንያቱን ያስቀምጣል።

በተጨማሪም በብልጽግናና ህወሐት መካከል "የስልጣን ሽኩቻ" ስላለ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመሃል ገብተው መፍትሔ ሊያመጡ እንደማይችሉና ተሰሚነት እንደማይኖራቸው በትግራይ ውጥስ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ በምሳሌነት በመጥቀስ ያስረዳል።

ፕሮፌሰር መረራ ፓርቲያቸው ብሔራዊ እርቅ እና ብሔራዊ መግባባት እንደሚያስፈልግ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲናገር መቆየቱን ያስታውሳሉ።

ብሔራዊ እርቁና መግባባቱ በማህበረሰብ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በመንግሥትና ተቃዋሚዎች መካከል እስካልተፈጠረ ድረስ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ አስቸጋሪ እንደሚሆን ፓርቲያቸው እንደሚያምን ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል።

አክለውም ለትግራይም ሆነ ለቀሪው ኢትዮጵያ ፍትሃዊ የሆነና በብሔራዊ መግባባት ላይ የተመሰረተ ምርጫ ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ።

አቶ ናትናኤል በበኩላቸው ፓርቲዎች በጋራ የፈረሙትን የቃል ኪዳን ሰነድ በማስታወስ የፌደራል መንግሥትን እያስተዳደረው ያለው ፓርቲ እና ትግራይ ክልልን እያስተዳደረ ያለው ፓርቲ ይህንን የቃል ኪዳን ሰነድ እንዲያከብሩ ግፊት ማድረግ ከፓርቲዎች እንደሚጠበቅ ይናገራሉ።

በቃል ኪዳን ሰነዱ በአሁኑ ሰዓት በሥራ ላይ ያለውን ሕገመንግሥት ማክበር፣ የሚደረጉ አንቅስቃሴዎች በሙሉ የሰላማዊ የሌሎችን ዜጎች መብት ያከበሩ እንዲሆን መስማማታቸውን ይጠቅሳሉ።

ኢዜማ ከዚህ አንጻር ይህ እንዲከበር ምክር ቤቱን እንደሚጎተጉት በመጥቀስ፣ በዚህ ጉዳይ ፓርቲዎች በጋራም ሆነ በግል ሁለቱ ወገኖች በውይይት ጉዳያቸውን እንዲፈቱ መጎትጎት እንደሚያስፈልጋቸው ይጠቅሳሉ።

የሁለቱ ወገኖች አለመግባባትም ወደ መሬት ወርዶ ተግባራዊ እንዳይሆን ፓርቲዎች ሚናቸውን መጫወት እንዳለባቸው ያሰምሩበታል።

አቶ አዳነ የሕወሓትና የብልጽግና ችግር የሁለቱ ፓርቲዎች ብቻ ሆኖ እንደማይቀር በመግለጽ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ መንግሥት እርምጃ እንዲወስድ ከመቀስቀስ ይልቅ ወደ ውይይት እንዲመጡ ተሰባስበው ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራሉ።

በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውስጥ የሚሳተፉ ከአንድ መቶ በላይ ፓርቲዎች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ አዳነ፣ እነዚህ ፓርቲዎች አንድ ልዑክ በማዋቀር የሁለቱ ፓርቲዎች ችግር እንዲፈታ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመር እንዳለባቸው ያስታውሳሉ።