1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የዐቢይ ኤኮኖሚ እንዴት ከረመ?

ረቡዕ፣ መጋቢት 25 2011

ባለሙያዎች ለአንገብጋቢ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ያተኮሩት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሐብት ቸል የሚል ሥጋት አላቸው። መድሐኒት መግዣ እንኳ አጥታ ለተቸገረችው ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ወራት 13 ቢሊዮን ዶላር ማግኘታቸውን ያስታወቁት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ የወሰዷቸው እርምጃዎች ግን በርካታ ናቸው።

https://p.dw.com/p/3GBuI
Brüssel EU Besuch Premierminister Abiy Ahmed Äthiopien
ምስል Office Prime Minister Ethiopia

የዐቢይ ኤኮኖሚ ክራሞት

ዐቢይ የኢሕአዴግን ሊቀመንበርነት፤ የኢትዮጵያን ጠቅላይ ምኒስትነት ሲሾሙ አገሪቱ ቋፍ ላይ ነበረች። ጠቅላይ ምኒስትሩ ትናንት ሥልጣን የጨበጡበትን አንደኛ አመት ሲዘክሩ "አምና በዚህ ጊዜ የአገሪቱ ቀጣይነት ልጡ የተራሰ ጉድጓዱም የተማሰ ይመስል ነበር" ሲሉ ወደ ኋላ መለስ ብለው አስታውሰዋል።

በእርግጥ ወቅቱ የውጥንቅጥ ነበር። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በርካቶችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት እና ለእስር የዳረጉ የተቃውሞ ሰልፎች እና ግጭቶች ኢትዮጵያን ንጠዋታል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትኩሳት እና አለመረጋጋት የውጭ ባለወረቶችን አሽሽቷል። ኢትዮጵያም መድሐኒት እንኳ የምትሸምትበት የውጭ ምንዛሪ እስከ ማጣት ያደረሰ ቀውስ ፊት ቆሞ ነበር።

Äthiopien landwirtschaftliche Erzeugnisse auf einem Markt
ምስል DW/M. Haileselassie

ዐቢይ ሥልጣን ሲይዙ ከጥቂት ዓመታት በፊት ፈጣን እየተባለ የተሞካሸው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ቅርቃር ውስጥ ገብቷል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ለአንገብጋቢ ፖለቲካዊ ጉዳዮች መፍትሔ ከመፈለግ ባሻገር ለምጣኔ ሐብቱ ምን አደረጉ? የምጣኔ ሐብት ባለሙያው እና በአማካሪነት የሚያገለግሉት አቶ ጌታቸው አስፋው "ኤኮኖሚው ላይ ተንቀሳቅሰዋል ተብሎ እንኳ ቢነገር አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስለገጠማት ተሯሩጠው ለዚህ አመት ለገቢ ንግድ የሚሆናትን አግኝታለች። አገሪቱን ወጥሮ የያዛት የሥራ አጥነት ሁኔታ እና ዋጋ ንረትን በተመለከተ ግን  ምንም የተወሰደ እርምጃ የለም። እንዲያውም ዋጋ ንረት ተባብሶ ቀጥሏል። የስራ አጥ ሁኔታም ተባብሶ ቀጥሏል" ሲሉ ይናገራሉ። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የተወሰነ ድርሻ ለመሸጥ የተላለፈው ውሳኔ ገና አለመጠናቀቁን የሚያስታውሱት አቶ ጌታቸው አስፋው "ባለሙያዎች እኔም ጭምር ጠቅላይ ምኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ለኤኮኖሚ ማሻሻያ ያሳዩት ትኩረት አናሳ ነው ብለን ነው የገመገምንው" ሲሉ ይናገራሉ።

አቶ ጌታቸው አስፋው እንዳሉት አገሪቷን ሰቅዞ ለያዛት የውጭ ምንዛሪ እጥረት መፍትሔ መሻት ከዐቢይ ቀዳሚ የቤት ሥራዎች አንዱ የነበረ ይመስላል። በትናትናው ዕለት ኢትዮጵያ በሰባት ወራት 13 ቢሊዮን ዶላር በልዩ ልዩ መንገዶች ማግኘቷን ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኩራት ተናግረዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ ገንዘቡን ያገኘችው ከመዋዕለ ንዋይ፣ ከብድር፣ ከእርዳታ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከላኩት እና ከአገልግሎት ዘርፎች ነው።

ኢትዮጵያ «ላለፉት መቶ ዓመታት በሰባት ወር 13 ቢሊዮን ዶላር አምጥታ አታውቅም» ያሉት ዐቢይ «በርካታ ኤልሲዎች ተከፍተው የግሉ ዘርፍ ከውጭ ሊያስገባ የሚፈልጋቸውን ዕቃዎች በወረፋ ምክንያት የነበረበትን ተግዳሮት ለመፍታት ስምንት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ለዚሁ ዘርፍ በዚህ ሰባት ወር ያወጣን መሆኑን በኩራት ልገልፅላችሁ እወዳለሁ» ሲሉም ተደምጠዋል።

Äthiopien Commercial Bank of Ethiopia in Addis Abeba
ምስል DW/E. Bekele

የመዋዕለ-ንዋይ እና ፐብሊክ ፖሊሲ አማካሪው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም «ጊዜው የርብርብ» መሆኑን ታዝበዋል። "በመንግሥትም በግሉ ዘርፍም በውጭ እርዳታ ለጋሾች በኩልም ሌሎች ድጋፍ በሚያደርጉ አካላትም የሚታየው ይኸ ዕድል መልካም ዕድል ነው የሚል አዎንታዊ አመለካከት አለ። እጅግ ብዙ መሰራት ያለባቸው የቤት ሥራዎች አሉ። ከፊትም የተደቀኑ ትላልቅ የሚባሉ ተግዳሮቶች አሉ።  እነሱን መቅረፍ የሚችል ሥርዓተ-መንግሥት መገንባት፤ ተቋማትን ማደራጀት ባጠቃላይ የአገሪቱ ፖለቲካል ኤኮኖሚ የሚመራበትን የአመራር ሥርዓት ማጠናከር ላይ ርብርብ የሚታይበት ኤኮኖሚ ነው የምመለከተው ሲሉ ያስረዳሉ።

አቶ ጌታቸው እንደሚሉት ዐቢይ ጠቅላይ ምኒስትር መሆናቸው ለረዥም ጊዜ በተቃውሞ ለታወከው ምጣኔ ሐብት የመጨረሻ እስትንፋስ ዘርቶበታል። በባለሙያው ዕይታ አመራራቸው በሕዝብ ዘንድ ያሉ ቅሬታዎች ለማዳመጥ ዝግጁነት ማሳየቱ ሌላው ተስፋን የጫረ ጉዳይ ሆኗል።  ይኸ ለገበያው ተዋናዮች ጭምር ትሩፋት ሆኖ ይታያል። አቶ ጌታቸው ተክለማርያም "ከመጀመሪያው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ንግግራቸው ጀምሮ ለኤኮኖሚው በቂ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚችሉ ያመላከቱባቸው ንግግሮች የኤኮኖሚ ተዋናዮቹ ላይ ተስፋቸውን የበለጠ እንዲጠናከር አድርጓል" ብለዋል።

በገበያው ፈርጣማ ጡንቻ በነበረው የብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ላይ የወሰዱት እርምጃ አቶ ጌታቸው መልካም ከሚሉት ጎራ ይመደባል። ኩባንያው ገበያ የማዛባት አቅም የነበረው፤ የግሉ ዘርፍ ሊከውናቸው የሚችላቸውን ሥራዎች በብቸኝነት የተቆጣጠረ እና በፖለቲካ ልሒቃኑ ጥበቃ የሚደረግለት ሆኖ ቆይቷል። የዐቢይ አስተዳደር የግል ዘርፉን ከውድድር የመግፋት አቅም የነበረውን ኩባንያ አመራሩን በመቀየር እና የውስጥ አሰራሩን በማሻሻል በምጣኔ ሐብቱ ውስጥ የነበረውን ሚና ቀይረዋል።

Äthiopien Addias Ababa - Isaias Afwerki - Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Ayene

ከኤርትራ ጋር የጀመሩት ዕርቅ በድንበር አካባቢዎች የሞተውን የንግድ እንቅስቃሴ አነቃቅቷል። ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች ልትጠቀም ትችላለች የሚል ተስፋም ሰጥቷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኤርትራን የአየር ክልል መጠቀም የቻለውም ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ተግባራዊ በሆነው የኢሕአዴግ ውሳኔ ነው። የንግድ ሕጉን ጨምሮ የሕግ ማዕቀፎችን መቀየር እና ማሻሻል እንዲሁም ተቋማትን መልሶ ማደራጀት ባለፉት አንድ ዓመት ውስጥ የታዩ ጥረቶች ናቸው።

የምጣኔ ሐብቱ መንገድ ከወዴት አለ?

እንደ ፖለቲካው ሁሉ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት የሚመራበት ፍኖተ ካርታ ከወዴት አለ? የሚል ጥያቄ በጠቅላይ ምኒስትሩ ላይ ይነሳል። ኢሕአዴግ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ላለፉት በርካታ ዓመታት የሚከተሉት የልማታዊ መንግሥት ሞዴል እና የፖለቲካዊ ፍልስፍናው አብዮታዊ ዴሞክራሲ አንዳቸው ከሌላቸው የማይነጣጠሉ ሆነው ቆይተዋል። አቶ ጌታቸው አስፋው "ይኸ መንግሥት የድሮው ኢሕአዴግ ተቀጥላ እንጂ አዲስ መንግሥት ስላልሆነ አዲስ የኤኮኖሚ መርሐ ግብር ይዞ አልመጣም። እሳቸውም ሥልጣን እንደያዙ ልማታዊ መንግሥት የሚለውን የድሮውን የኢሕአዴግ አቅጣጫ ይዤ ነው የምጓዘው ነው ያሉት። ምን አልባት የዛሬ አመት ምርጫ ሲካሔድ ሌላ መርሐ-ግብር ቀርጸው ሊመጡ ይችሉ ይሆናል" ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው ተክለማርያም ኢትዮጵያን የወዘወዛት የሦስት ዓመታት ሕዝባዊ ተቃውሞ በዋንኛነት ምጣኔ ሐብቷ በፍጥነት ለሚያድገው የሕዝብ ቁጥር በቂ እና ተመጣጣኝ የሥራ ዕድል መፍጠር ባለመቻሉ የተቀሰቀሰ እንደሆነ ያምምናሉ። አቶ ጌታቸው «መንግሥት ለሕብረተሰቡ አገልግሎት የሚያቀርብበት ጥራት፣ ተደራሽነት እና ፍጥነት የተጎተተ እና ኋላ ቀር መሆኑ ሕዝብ የበለጠ ተስፋ እንዲቆርጥ አድርጎታል» ሲሉም ይናገራሉ።  ይኸው ጉዳይ ኢትዮጵያውያንን በተለይ ወጣቶችን ለተቃውሞ አደባባይ አውጥቷቸዋል የሚሉት አቶ ጌታቸው ጠቅላይ ምኒስትሩ ሥልጣን ከያዙ በኋላም ለምጣኔ ሐብቱ ትኩረት ተሰጥቶታል የሚል ዕምነት የላቸውም። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው «የአገሪቱን ሰላም እና የኅብረተሰቡን ደኅንነት ለማረጋገጥ ቅድሚያ መሰጠቱ» አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ግን ተረድተዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ