አሜሪካ ከቤተሰቦቻቸው የነጠለቻቸው 545 ህፃናት ወላጆችን ማግኘት አልተቻለም ተባለ

አንድ ህፃን ድንበር ሲሻገር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሜሪካ በሜክሲኮ ድንበር ወደ አገሯ ዘልቀው ሲገቡ ከቤተሰቦቻቸው የነጠለቻቸው 545 ህፃናት ወላጆች መጥፋታቸው ተነገረ።

ከነዚህም ውስጥ 2/3ኛ የሚሆኑት ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጋቸውንም ከፍርድ ቤት ሪፖርት መረዳት ተችሏል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ከልጆቻቸው ጋር በግድ የተለያዩ ሲሆን፤ በርካቶችም ማውገዛቸውንና ቁጣም ተከትሎ ነው ዋይት ሃውስ ከሁለት አመት በፊት ያወጣውን ፖሊሲ ያላላው።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝም ቤተሰቦቻቸውን ለመፈለግ መጓተት እንደፈጠረም ተገልጿል።

በሜክሲኮ በኩል የሚገቡ ስደተኞችን በጥብቅ የመቆጣጠርና የመግታት ፖሊሲ የወጣው ከሁለት አመታት በፊት ቢሆንም አስተዳደሩ ልጆችና ቤተሰቦቻቸውን የመነጣጠል ሚስጥራዊ ፕሮግራም የጀመረው ከሶስት አመታት በፊትም እንደሆነ ተገልጿል።

ጥብቅ የተባለው የስደተኞች ፖሊሲ መታወጁም ተከትሎ ህፃናት በመቆያ ማዕከል ውስጥ የቤተሰቦቻቸውን ስም እየጠሩ ሲያለቅሱ እንዲሁም ኢ-ሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ ታጉረው የሚያሳዩ ፎቶዎችና ድምፆች መውጣታቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጣን በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በአለም አስከትሏል።

ከሁለት አመት በፊትም የአሜሪካ ሲቪል ነፃነት ማሕበር ክስ መስርቶ የአሜሪካ ዳኛ ስደተኞች ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በ30 ቀናት እንዲገናኙ ወስኖ ነበር። በዚህም መሰረት በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች በሳምንታት ውስጥ መገናኘት ችለዋል።

ሆኖም በሚስጥራዊው ፕሮግራም ከሶስት አመት በፊት የተለያዩት ቤተሰቦችና ልጆቻቸው በዚህ የፍርድ ቤት ውሳኔ ብያኔ አላገኙም ነበር። የነዚህ ቤተሰቦችና ልጆቻቸው ጥምረት ውሳኔ ያገኘው ባለፈው አመት ነበር። በዚህም ወቅት ተለያይተው ከነበሩት 1 ሺህ 30 ህፃናት መካከል የተገኙት ቤተሰቦች 485 ብቻ ናቸው።

ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘትም እልህ አስጨራሽ ፍለጋ መደረጉንም የአሜሪካ ሲቪል ነፃነት ማሕበርና የአሜሪካው ፍትህ ዲፓርትመንት ባቀረቡት የፍርድ ቤት ሪፖርት ተመልክቷል። የመጡባቸውን አገራትም ላይ በመሄድ መሬት ላይ አሰሳ መደረጉም ተገልጿል ሆኖም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እክል ፈጥሯል ተብሏል።

"ቤተሰቦቹ ሊገናኙ ይገባል አስተዳደሩም ለዚህ ተጠያቂ ነው። ኃላፊነቱንም ሊወስድ ይገባል" በማለት በማህበሩ አቃቤ ህግና የቤተሰቦቹን ጉዳዮች በመሪነት የያዙት ሊ ጌለርንት በመግለጫቸው አስፍረዋል።

ሊ ጌሌርንት እያንዳንዱ ልጅ ከቤተሰቦቹ ጋር እስኪገናኝ ድረስም ፍለጋቸውም እንደሚቀጥል ገልፀው "እነዚህ ህፃናት ለአመታት ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተው የቆዩ ናቸው። አንዳንዶቹ ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲለያዩ በጣም ጨቅላም ነበሩ" ብለዋል።

ልጆችና ቤተሰቦችን መለየት ትልቁ የትራምፕ አስተዳደር "ጥቁር ነጥብ" ነው ብለዋል።

በወቅቱም ፕሬዚዳንት ዶናልደፍ ትራምፕ ምንም እንኳን ልጆችን ከቤተሰቦቻቸው መውሰድ ባይፈልጉም ነገር ግን "ቤተሰቦች በህገ ወጥ መንገድ አገራችን ገብተዋል ብለን ስንከሳቸው ልጆቻቸውን ልንወስድ ይገባል" በማለትም ተከራክረዋል።