Fana: At a Speed of Life!

ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ክልላዊ መንግስት ከፍጥጫ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገራትን የፖለቲካ ሁኔታ በመከታተል የግጭት ስጋቶችን ይፋ የሚያደርገው ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ክልላዊ መንግስት ከፍጥጫ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጠይቋል፡፡
ቡድኑ ይፋ ባደረገው ሰነድ የትግራይ ክልል መንግስት በፌደራሉ መንግስት ህገ ወጥ የተባለ ምርጫ ካካሄደ በኋላ በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግስት መካከል ያለው ፍጥጫ መካረሩን አስታውቋል፡፡
እንዲሁም ቡድኑ ህገ ወጡ ምርጫ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውድቅ ከሆነ እና እንዳልተደረገ የሚቆጠር መሆኑ ከተወሰነ በኋላ የፌደራል መንግስት በህገ ወጡ ምርጫ ከተመረጠው የትግራይ ክልል ምክር ቤት እና ካቢኔ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲቋረጥ ማድረጉንም ቡድኑ በረቂቅ ሰነዱ አስታውሷል፡፡
ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ፍጥጫ ላይ ያሉት የፌደራል እና የትግራይ ክልል መንግስታት ለውይይት እና ንግግር ቅድሚያ እንዲሰጡ በጠየቀበት ሰነድ የፌደራሉ መንግስት የድጎማ በጀት ክልከላውን ለተወሰነ ጊዜ ከመተግበር እንዲያዘገይ እና የትግራይ ክልል መንግስትም የድርድር መሰናክል ከሚሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ተላቆ ለድርድር ዝግጁ እንዲሆንም አሳስቧል፡፡
የፌደራል መንግስትም ወታደራዊ እርምጃዎችን ከመውሰድ እንዲቆጠብ እና እንዲታገስ የጠየቀው ቡድኑ የትግራይ ክልል ባለስልጣናትም የጦር ነጋሪት ከመጎሰም እንዲታቀቡ ጠይቋል።
በዳዊት መስፍን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.